ጤና ጥበቃና ህክምና ለጥገኝነት ጠያቂዎች

Hälso- och sjukvård för asylsökande – amhariska

ስዊድን ውስጥ ጥገኝነት የጠየቃችሁ ሰዎች ሁሉ ለአስቸኳይ የጤና፥ የጥርስ ሕመምና መቆየት ለማይችል በሽታ ህክምና የማግኘት መብት አላችሁ።

ስዊድን ውስጥ ጤና ጥበቃና የህክምና ጉዳይ የሚመራው በአውራጃዎች ወይም በክፍለ ሀገር አስተዳደሮች ነው። እነሱም በመላ ሃገሪቱ ይገኛሉ።

ሲታመሙ ወይም አንዳች ጉዳት ሲደርስብዎት መጀመሪያ የሚሄዱት ወደ ጤና ጣቢያ (vårdcentral) ነው። አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጤና ጣቢያ ከመሄድዎ በፊት ቀጠሮ መያዝ ይኖርብዎታል። ቀጠሮ ሲይዙ አስተርጓሚ እንደሚያስፈልግዎትም ያሳውቁ። በድንገት ከታመሙና አምቡላንስ የሚያስፈልግዎት ሁኔታ ላይ ከሆኑ የአስቸኳይ ጉዳይ ቁጥር 112 ይደውሉ።

በዚህ ጽሁፍ ውስጥ፥ ወደታች ወረድ ብለው፥ የሚያስፈልጎትን ህክምና እንዴት ማግኘት እንደሚችሉና የህክምና ምክርም የት ማግኝት እንዳለብዎት የሚጠቅሱ መረጃዎች ያገኛሉ።

የመታከም መብት

ስዊድን ውስጥ ጥገኝነት ሲጠይቁ ለድንገተኛ የጤና፥ የጥርስ ህመምና መቆየይ ለማይችል ህመም ህክምና የማግኘት መብት ይኖርዎታል። ማግኘት የሚገባዎን የህክምና ዓይነት የሚወስነው የክፍለ ሀገር ወይም አውራጃ አስተዳደሩ ነው። የወሊድ ሕክምና፥ ፅንስ የማስወረድ ሕክምና፥ ፅንስ የመከላከል ምክር፥ የማህጸን ህክምና እንዲሁም ተላላፊ በሽታዎች እንዳይስፋፉ ለመከላከል በወጣው ሕግ መሰረት፥ ተላላፊበሽታዎችን የመታከም መብትም አለዎት። (ሕጉ፥ ተላላፊ በሽታዎች እንዳይስፋፉ ለመከላከል የወጣ ሕግ ተብሎ ይጠቀሳል።)

ጥገኝነት ጠያቂ ልጆችና ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ታዳጊዎች እንደማንኛውም በስዊድን እንደሚኖሩ ልጆች ተመሳሳይ የጤናና የጥርስ ህክምና መስተንግዶ የማግኘት መብት አላቸው። ሕክምናው ለልጆች፥ በአብዛኛው ማለት ይቻላል፥ ነፃ ሲሆን እንደሚኖሩበት አካባቢ፥ በአንዳንድ ቦታዎች ለየት ሊል ይችላል። መድሃኒት በሃኪም የታዘዘ እስከሆነ ድረስ ነፃ ነው።

ከሃኪም ቤት በሚገናኙበት ጊዜ አስተርጓሚ የማቆም መብት ስላለዎት፥ ቀጠሮ ሲይዙ አስተርጓሚ እንደሚያስፈልጎት ይናገሩ።

የጤና ምርመራ

ሁሉም ጥገኝነት ጠያቂ የጤና ምርመራ እንዲያደርግ ግብዣ ይቀርብለታል። የጥገኝነት ጥያቂ እንዳስገቡ፥ ብዙ ሳይቆይ፥ በነጻ የጤና ምርመራ እንዲያደርጉ የሚያሳስብ ጥሪ ይደረግልዎታል።

የጤና ምርመራው የጥገኝነት ጥያቄዎ ላይ ምንም ተጽዕኖ አይኖረውም። ምርመራው ለርስዎ ጤና ተብሎ፥ ምናልባት ህክምና የሚያስፈልግዎ ከሆነ ሳይውል ሳያድር ቶሎ ርዳታ እንዲያገኙ በማለት የሚደረግ ነው።ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት ስለ ጤናዎ ጥያቄዎች፥ ስለ ምርመራ ናሙና መስጠትና በስዊድን ስላለው የጤናና ህክምና መረጃ ያገኛሉ። የጤና ጥበቃ ሰራተኞች ከስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም። ያዩትና የሰሙትንም ለማንም እንዳያሳልፉ ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው።

ድብድብና ጾታዊ ጥቃት

ብዙ ጥገኝነት ጠያቄዎች በአገራቸው በነበሩበት ጊዜና ከአገራቸው ወጥተው በሚሰደዱበት ወቅት ለድብድብና ለጾታዊ ጥቃት ይጋለጣሉ። በዚህ የተነሳ እነዚህ ሰዎች አካላዊና ስነልቦናዊ ደህንነታቸው በጎ ሁኔታ ላይ ላይሆን ይችላል። በአካላቸው ላይ ከሚደርሰው ጉዳት በተጨማሪ ለምሳሌ ድብርት፥ ሃዘንና የእንቅልፍ ችግርም ያጠቃቸዋል። የህክምና ባለሙያዎችን በሚያገኙበት ጊዜ ምን ዓይነት ችግር እንዳለብዎት ቢያስረዱ ትክክለኛውን ህክምና እንዲያገኙ ይረድዎታል።

በስዊድን ማንኛውም ዓይነት ነውጥና የወሲብ ጥቃት በሕግ የተከለከለ ነው። እንዲህ አይነት በደል በሚፈጸምበት ጊዜ ተጠያቂው በዳዩ እንጅ፥ በደል የተፈጸመበት ገለሰብ ለነውጥ ወይም ለጾታዊ ጥቃት በመጋለጡ ምክንያት አይቀጣም። ሕጉ በባለጉዳዮቹ መሃል ዝምድና ቢኖርም ባይኖም ይሰራል፥ ለምሳሌ በትዳር ውስጥና በመሃላቸው ልጅ እንኳ ቢኖርም አስገድዶ መድፈር የሚያስጠይቅ ጥፋት ነው።

የሴቶች ግርዘት

ሴቶችን የመግርዝ ልማድ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች እንደሚካሄድ እናውቃለን። ይህ ማለት የአንዲት ልጃገረድ ወይም ሴትን ብልት በስለት መሸርከት ማለት ነው። የሴትን ብልት መሸርከት በስዊድን የተከለከለ ሲሆን ድርጊቱም እንደ አንድ ከባድ ወንጀል ይታያል። ለዚህ ዓይነቱ በደል የተዳረገች ሴት አካላዊና ስነልቦናዊ ችግር ውስጥ ትወድቃለች። እንዲህ ዓይነት በደል ተፈጽሞብሽ ከሆነ ወይም በልጅሽ ላይ ደርሶ ከሆነና በመካያው የጤና ችግር ካለ የህክምና እርዳታ ማግኘት ይቻላል። የጤና ምርመራ ስታደርጊ፥ ከጤና ባለሙያዎች ጋር ወይም ባቅራቢያሽ ካለው የጤና ማዕከል (vårdcentral) ጋር ተነጋገሪ።

በወስባዊ ግንኙነትየሚተላለፉ በሽታዎች

በወሲባዊ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ዕውቀት የማግኘት መብት እንዳልዎት ሁሉ በሽታው ወደ ሌሎች እንዳይጋባም ስለማድረግ ግንዛቤ የማግኘትም መብት አለዎት። በወሲባዊ ግንኙነት ከሚተላለፉ በሽታዎች ለምሳሌ ያህል ጥቂቱን ብንገልጽ፥ ”ክላምዲያ”፥ ”ሄፓቲት”፥ ”ጨብጥ” እና ”ኤችአይቪ” ይገኙበታል። እንደነዚ ዓይነቱ በሽታዎች ያለብዎት መሆንዎን ካወቁ፥ በስዊድን ሕግ መሰረት፥ በሽታውን ወደ ሌላ ሰው እንዳያጋቡ፥ እርስዎም ተገቢውን ህክምና እንዲያገኙ፥ ለጤና ባለሙያ ማሳወቅ ይኖርብዎታል። የጤና ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት ለሰራተኞቹ ችግርዎን ይንገሩ። በሽታው እንደሌለብዎት እርግጠኛ ካልሆኑም የጤና ሰራተኞቹ የምርመራ ናሙና ወስደው ያረጋግጣሉ።

ፅንስ መከላከያና የመሃጸን ጤና ጥበቃ

ስዊድን ውስጥ ጥገኝነት ለጠየቁ ሁሉ የመሃጸንና የወሊድ ህክምና በነጻ ይሰጣል። ከጽንስ ማስወረድ ጋር የሚያያዝ ህክምናም እንዲሁ በነጻ ይሰጣል።የፅንስ መከላክያን በተመለከተም በነጻ ምክር በማግኘት ራስዎ በፈቃድዎ ወላጅ ለመሆን የመወሰን መብት አልዎት። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ራሳቸውንና ሌላውን ካለአስፈላጊ ፅንስ ለመከላከል የሚያስችል መረጃ የማግኘት መብት አላቸው።

ብዙ ፅንስ መከላከያ ዘዴዎች አሉ። ኮንዶሞችን ከመድሃኒት መሸጫ ተቋማትና ከምግብ መሸጫ ሱቆች መግዛት ይችላሉ። ሌላ ዓይነት ፅንስ መከላከያ ካስፈለገ ሃኪም ወይም የመሃፀን ጤና ባለሙያ ለርሶ የሚስማማውን ለይተው ሊያዙልዎት ይችላሉ። በሃኪም የታዘዘ ፅንስ መከላከያ ከ18 ዓመት ዕድሜ በታች ለሆኑ ነጻ ነው።

እርጉዝ ከሆንሽ የጤና ምርመራ ስታደርጊ ከሰራተኛቹ ጋር ተነጋገሪ፥ አልያም በአቅራቢያሽ ካለው ሆስፒታል፥ የእርጉዞች ጤና ጥበቃ ክፍልን ተገናኝተሽ ስለሚያስፈልግሽ ህክምና ተነጋገሪ።

ስነልቦናዊ ጤንነት

የጥገኝነት ጥያቄዎን መልስ በሚጠብቁበት ወቅት ወደ ፊት ሊመጣ ስለሚችለው መጨነቅ ያለ ነው። ብዙ ጥገኝነት ጠያቄዎች በሚገጥማቸው ነገርና ለቤተሰቦቻቸውም በማሰብ ስለሚጨነቁ ጤናቸው ላይ ጫና ይኖራል። ሁኔታው በሰዎች ጤና ላይ የሚያደርሰውን ችግር ዓይነት ለመግለጽ ያህል፥ ድብርትን፥ የዕንቅልፍ ማጣትን ወይም የሃዘንና የድካም ስሜትን እንደምሳሌ መጥቀስ ይችላል።

በዚህ ችግር የሚጠቁ ከሆነ በሚኖሩበት አካባቢ ካለው የጤና ማዕከል እርዳታና ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ። የጤና ምርመራ ሊያደርጉ ወደ ጤና ማዕከል ሲሄዱ ለሰራተኞቹ ይንገርዋቸው። የልጅዎ ጤና በመታወኩ ምክንያት የሚጨነቁ ከሆነ የህፃናት ጤና ክፍል (barnavårdscentralen) ካሉ ሙያተኞች ጋር ወይም ልጅዎ ከሚማርበት ት/ቤት ጋር ይነጋገሩ።

የብቃት ውሱንነት

የጤና ምርመራ ለማድረግ በሚመጡበት ጊዜ የብቃት ውሱንነት እንዳለብዎት ወይም ይኖርብኛል ብለው ይሰጉ እንደሆን ለባለሙያዎቹ የማሳወቅ ዕድል አለዎት። ይህ ማለት የአካል እንቅስቃሴ ደረጃ መውረድ፥ የስነ~አእዕምሯዊ እና የዕውቀት ዝቅ ማለትን ጭምር ይመለከታል።

የጥገኝነት ጥያቄ ለማቅረብ የብቃት ውስንነትዎ ሃስብዎን ለመግለጽ የሚያስቸግርዎ ከሆን እርዳታና ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል። የብቃት ውስኑነት በአገሪቱ የመኖሪያ ፍቃድ እንዳያገኙ አያደርግም።

የብቃት ውሱንነት እያለብዎት በስዊድን የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በስዊድን ማህበራዊ ኑሮ ውስጥ በቀላሉ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስችል ድጋፍ የማግኘት መብትዎ የተጠበቀ ነው።

የጥርስ ህክምና

እናንት በአዋቂ ዕድሜ ክልል ውስጥ ያላችሁ፥ አስቸኳይ የጥርስ ህመም ህክምና የማግኘት መብታችሁ የተጠበቀ ነው። ህመምዎ አስቸኳይ መሆኑንና ምን ዓይነት ህክምና ማድረግ እንደሚገባዎት የሚወስነው የጥርስ ሃኪሙ ነው። ልጆች ግን አስቸኳይ ህክምና ብቻ ሳይሆን የጥርስን ጤና ለመጠበቅ የሚደረግ መደበኛ ህክምናም ከጥርስ ሃኪም ቤት ማግኘት ይችላሉ።

የጥርስ ህክምና ለማድረግ ወደ ህዝባዊ የጥርስ ህክምና ማዕከል (folktandvården) ወይም የክፍለ ሃገሩ ጽ/ቤት ወደ ሚመራዎት ሌላ የጥርስ ሃኪም ዘንድ መሄድ ይችላሉ።

ዓይን ምርመራ እና መነጽር

መነጽር ያስፈልገኛል ብለው ካሰቡ፡ የስደተኞች መቀበያ ክፍልዎን ያነጋግሩ፥ እና ለዓይን ምርመራ እና መነጽር፥ ልዩ የገንዘብ እርዳታ ያመልክቱ። የዓይን ምርመራ ማድረግ እንዳለቦት የሚወስነው፥ በስዊድን የስደተኞች ኤጀንሲ የጉዳይ ሥራ አስኪያጅ ነው። የጸደቀ የአይን ምርመራን በተመለከተ ውሳኔ ሲደርስዎ፥ ከዓይን ሐኪም ጋር ቀጠሮ መያዝ ይችላሉ፥ እና ምርመራው በሶስት ሳምንታት ውስጥ ማድረግ ይኖርብዎታል። የዓይን ሐኪም ከምርመራው በኋላ መነፅር ያስፈልግዎታል ብሎ ውጤቱን ካረጋገጠ፥ የስዊድን የስደተኞች ኤጀንሲ የሚከፍልው መነጽር ያዛሏታል።

መድሃኒት

ከፋርማሲ (apoteket) የተለያዩ ዓይነቶች መድሃኒቶችና የጤና ምርቶች መግዛት ይችላሉ። ሃኪምዎ በማዘዣ ላይ የጻፍዎለትን መድሃኒት ከፋርማሲ ማውጣት ይችላሉ። የታዘዘልዎትን መድሃኒት ሊያወጡ ሲሄዱ LMA-kort የሚባለውን መታወቂያ ወረቀትዎን መያዝ አይርሱ። መታወቂያዎን ከያዙ ሃኪም ያዘዘውን አብዛኛዎቹን መድሃኒቶች በቅናሽ ዋጋ ያገኟቸዋል።

ስለ ጤናና ህክምና ተጨማሪ ማብራሪያ

  • በዚህ ደረገጽ www.1177.se External link, opens in new window. ውስጥ ስለተለያዩ በሽታዎችና ስለ ስዊድን የጤና ጥበቃ ተቋማት አሰራር በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃ ያገኛሉ። እዚያ ላይ በአቅራቢያዎ ያሉ የጤና ማዕከላትንና የጥርስ ህክምና ቤቶች ስልክ ቁጥሮች ያገኛሉ።
  • ወደ ”ቮርድጋይደን” (Vårdguiden) በዚህ ቁጥር1177መደወል ይቻላል። ሲደውሉ ጥያቄዎን መመለሰና ምክር መስጠት ከሚችሉ የጤና ባለሙያዎች ጋር ይገናኛሉ። የጤና ባለሙያዎቹ የሚያስፈልግዎትን የህክምና ዓይነትና ህክምናውንም የት ሄደው ማግኘት እንድሚችሉ ይነግርዎታል። 
  • በዚህ https://www.rfsu.se/upos External link, opens in new window. ድረገጽ ውስጥ፡ ስለ ገላ፡ ወሲብነትና ጤንነት፡ በበለጠ ለማወቅ የሚሹ የተዘጋጁ ኣጫጭር የመረጃ ፊልሞች ይገኛሉ። እነዚህ ፊልሞች በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ቀርቧል። ከዚሁ መሃል ለምሳሌ፡ ስለ ክልኣተ-ወሊድ፡ ስለ ልጅ መውለድና ስለ እርግዝና የተዘጋጁ ፊልሞች ማግኘት ይችላሉ።
  • በዚህ ድረገጽ http://www.youmo.se/ External link, opens in new window. ለታዳጊዎች የሚሆን ስለጤና፥ ስለ ግንኙነት፥ ስለ ወሲብና ሌላም ጉዳዩች የሚገልጽ መረጃ በበርካታ ቋንቋዎች አለ። 
  • ”የሴቶች ሰላም መስመር/ክቪኖ-ፍሪድስ-ሊንየ” (Kvinnofridslinjen) ለዛቻ፥ ለዱላ፥ ለስነልቦናዊና ጾታዊ ጥቃትየተዳረጉ ሴቶች ምክርና ድጋፍ ያቀርባል። 020-50 50 50 ይደውሉ። አስተርጓሚ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ይሰየምሎታል። ለተጨማሪ መረጃ kvinnofridslinjen.se ይጎብኙ፥መረጃዎች በበርካታ ቋንቋዎች አሉ። 
  • በሴቶች ማስተናገጃ ጽ/ቤት ወይም በማረፊያው ሥፍራ ያሉ ሰራተኞች ተጨማሪ መረጃ እንዲያገኙና በሚኖሩበት አካባቢ ትክክለኛ ህክምና የት ሄደው ማግኘት እንደሚችሉ ሊገልጹልዎት ይችላሉ።

የህመምተኛ መጓጓዣ

በጤናዎ ምክንያት ወደ ህክምና ቦታ ራስዎ መሄድ የሚችሉበት ሁኔታ ከሌለ፥ የህመምተኛ መጓጓዣ (sjukresa) ማዘዝ ይቻላል። በጤናዎ ምክንያት ወደ ጤና ማዕከል ወይም ወደ ሆስፒታል በግልዎ ከተጓዙ፥ የተጓዙበትን ወጪ ማካካሻ ገንዝብም ሊያገኙ ይችላሉ። የህመምተኛ መጓጓዣ እንደሚገባዎት የሚወስነው ህክምና የሰጥዎት ባለሙያ ነው። በሚኖሩበት ክፍለ ሀገር ውስጥ ስላለው ደንብ የበለጠ መረጃ ለማግኘት 1177 Vårdguiden ይደውሉ።

ለተጨማሪ መረጃ www.1177.se/sa-fungerar-varden/sjukresor-och-fardtjanst/sjukresor/ (በስዊድንኛ ብቻ) External link, opens in new window.

 (LMA-kort) መታወቂያዎን ይያዙ

አንድ ጤና ማዕከል ሲጎበኙም ሆነ መድሃኒት ለማውጣት ወደ ፋርማሲ ሲሄዱ መታወቂያዎን (LMA-kort) ማሳየት ይኖርብዎታል። መታወቂያው ለማውጣት ካልደረሱ ግን ጥገኝነት የጠየቁበትን ደረስኝ ማሳየት ይችላሉ። LMA-kort የሚባለውን መታወቂያ ሲያሳዩ የታካሚነት ክፍያው ቅናሽ የሚሆንበት አጋጣሚ ይኖራል። በሃኪም የታዘዘሎትን መድሃኒትም ሲገዙ መታወቂያዎን LMA-kort ካሳዩ ለአብዛኛዎቹ መድሃኒትቶች የሚከፍሉት ዝቅ ያለ ዋጋ ነው።

Last updated: