LMA-ካርድ ለጥገኝነት ፈላጊዎች
LMA-kort för asylsökande – amhariska
ኤል. ኤም. አ. (LMA)፡ ጥገኝነት ለሚጠይቁ የወጣ ህግ ማለት ”lagen om mottagande av asylsökande” ማለት ነው። ኤል ኤም አ ካርድ ጥገኝነት ጠያቂ መሆንዎን የሚያሳይ ፎቶዎ ያለበት ፕላስቲክ ካርድ ነው.።
ስዊድን ውስጥ ጥገኝነት ሲጠይቁ ፎቶግራፍ ይነሳሉ. ከዚያ በኋላ ኤል. ኤም. አ. ካርድ ያገኛሉ። ካርዱ መታወቂያ ወረቀት (id-kort) አይደለም። ጥገኝነት መጠየቅዎን የሚመሰክርና ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ ስዊድን ውስጥ መቆየት የሚችሉ መሆንዎን የሚገልጽ ካርድ ነው። ካርዱ ግላዊ ሲሆን፥ ቀደም ብሎ ጥገኝነት ሲጥይቁ የተሰጥዎትን ደረሰኝ የሚተካ ነው። ኤል. ኤም. አ. ካርድ ጥገኝነት ጠይቀው ባሉበት ወቅት የመስራት መብት ያልዎት መሆንዎን የሚገልጽ AT‑UND ተብሎ የሚጠራ መረጃም ይዟል።
ኤል. ኤም. አ. ካርድዎን ሁሌ ከርሶ አይለዩ
ኤል. ኤም. አ. ካርድዎ ላይ ካለው ፎቶ ሥር የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት ጋር ያልዎት ጉዳይ ቁጥር ወይም ፋይል ቁጥር አለ፣ ከስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት ሰራተኛ ጋር በሚነጋግሩበት ወቅት ይህን ቁጥር ቢይዙ መልካም ነው። በዚህ ቁጥር አማካይነት የእርስዎን ጉዳይ የያዙ ሰነዶችን በቀላሉት ማውጣት ይቻላልና።
ባለሥልጣናትን በሚገናኙበት ወቅት ወይም ለአንድ አሰሪ የመቀጠር መብት ያለዎት መሆንዎን ለማረጋገጥ ሲፈልጉ ኤል. ኤም. አ. ካርድዎን ያሳዩ። ሥራ አግኝተው፣ የባንክ ሂሳብ መክፈት ካስፈለግዎት ደግሞ ኤል. ኤም. አ. ካርድዎን ለባንኩ ማሳየት ይኖርብዎታል።
በአንዳንድ አጋጣሚዎች የኤል. ኤም. አ. ካርድዎ ከውጭ አገር የተላከልዎትን ፓኬት ወይም ከስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት የሚላክልዎትን የአደራ ደብዳቤ ከፖስታ ቤት ለማውጣት እንደ መታወቂያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
በአንድ ሃኪም የሚታዘዝሎትን አብዛኞቹን መድሃኒቶችም የኤል. ኤም. አ. ካርድዎ ለመድሃኒት ቤት በማሳየት፣ ቅናሽ ዋጋ ከፍለው ማግኘት ይችላሉ። አንድ የጤና ተቋም በሚጎበኙበት ግዜ፣ የሚከፍሉትን የህመምተኛ ክፍያ አንዳንድ ግዜ የኤል. ኤም. አ. ካርድዎ በማሳየት ቅናሽ ክፍያ ሊከፍሉ ይችላሉ።
ለተጭማሪ መረጃ ’ጤና ጥበቃ ለጥገኝነት ጠያቄዎች’ ያንብቡ፣ sjukvård för asylsökande
የኤል. ኤም. አ. ካርዱ የሚጸናበት ግዜ
ካርድዎን በአዲስ መቀየር አያስፈልጎትም። ይሁን እንጂ በጥገኝነት ዘመንዎ ውስጥ እስካሉ ድረስ በየግዜው ወደ ስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት በመምጣት ካርዱ የሚጽናብትን የግዜ ገደብ ማራዘም ይኖርብዎታል።
የኤል. ኤም. አ. ካርድ የሚታደሰው በዲጂታል ሲስተም ነው፣ እናም የስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤትን በጎበኙ ቁጥር፣ በማንኛውም ምክንያት ቢመጡም፣ ካርድዎ የሚጸናበት ግዜ በሶስት ወራት ይራዘማል። ነገር ግን ለጥቂት ወራት ያህል ጽ/ ቤቱን ድረስ መጥተው ሳይጎበኙን ቢቆዩ፣ ካርድዎ የሚጸናበት ግዜ ከማለቁ ሁለት ሳምንት ቀደም ብሎ እንድ ማስታወሻ እንዲደርስዎት ይደረጋል። ልጆችዎም መራዘም የሚያስፈልገው ኤል. ኤም. አ. ካርድ ያላቸው ከሆነ፣ እነሱም ከእርስዎ ጋር ወደ ስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት መምጣት ይኖርባቸዋል።
ኤል. ኤም. አ. ካርድ ኪው አር-ኮድ (QR-kod) አለው
ከጃንዋሪ 1/ 2022 ዓ ም በኋል የሚወጣው አዲሱ ኤል. ኤም. አ. ካርድ የኪው አር-ኮድ ማንበቢያ መሳሪያ ያለው ሁሉ ካርዱ የሚጽናበት ግዜ ያልወደቀ መሆኑን እና የመሥራት መብት AT-UND ያለዎት መሆንዎን በቀላሉ መመርመር የሚያስችል ነው። ከዚህ ውጭ ሌላ እርስዎን የሚገልጽ ምንም መረጃ የለውም፣ በምርመራ የሚገኘው መረጃም የትም አይቀመጥም።
የመስራት መብት (AT-UND) እንዲሰጥዎት ሲወሰን፣ ውሳኔው በቀጥታ ኤል. ኤም. አ. ካርድዎ ውስጥ ይመዘገባል፣ እናም ቀጣሪዎ ኮዱን በኪው አር ኮድ ስካነር አማካይነት አንብቦ መመርመር ይችላል።
ኤል. ኤም. አ. ካርድዎ ቢጠፋብዎት
የርሶ ኤል.ኤም.ኣ. ካርድ (LMA-kort) ቢሰረቅ ወይም ቢጠፋ፥ ወደ የርሶ “የስደተኞች መቀበያ ጽ/ ቤት” ወይም ወደ “አገልግሎት-መስጫ ማእከል” በመምጣት፥ ማመልከቻ ማቅረብ ይግባዎታል። ከዛ በኋላ “ሚግራሾንስቨርከት” ካርድዎን ይሰርዝና፥ ኣንድ ኣዲስ ያዝዝልዎታል።
ካርዱን ስለ መመለስ
ከየስደተኞች ጉዳይ ጽ/ ቤት መዝገብ ውስጥ ሲሰረዙ ኤል. ኤም. አ. ካርድዎን ይመልሳሉ። የመኖሪያ ፈቃድ ቢያገኙ ወይም በማንኛውም ምክንያት ድጎማ የማግኘት መብትዎ ቢቋረጥ ወይም ከስዊድን ቢወጡ ካርዱን መመለስ ይኖርብዎታል።